ወገንተኛው፣ መርህ የለሹና ከጅምሩ የከሸፈው የአፍሪቃ ሕብረት ሽምግልና በኢትዮጵያ

በሙሉጌታ ገብረሕይወት (ዶ/ር)፣ መስከረም 20-2014

ትርጉም- አገኘሁ እና ንጉሱ

 ከተባበሩት መንግስታት መመሪያዎች አንዱ  እንደሚለው ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማስተዳደር እና ከሁሉም በላይ ግጭቶችን ለመፍታት ሽምግልና በጣም ውጤታማ ከሆኑ ዘዴዎች አንዱ ነው።

ይህ እንዲሆን ግን ትልቅ ስምና ዝና  ያለውን ሸምጋይ ከመሰየም በላይ የሆነ ድርጊት ይጠይቃል። ይህ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ቢያንስ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች በአሸማጋዩ ድርጅትና ግለሰብ ላይ መስማማት አለባቸው።

በግጭቱ ውስጥ ያሉት ተፋላሚዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ይሁንታ ሳይኖራቸው  በመልካም ስሜት ለድርድር ሊቀመጡም ሆነ  ለሂደቱ ቁርጠኛና  ለውጤቱም ተባባሪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሽምግልና መመሪያ የአንድን ሽምግልና ሒደት በተመለከተ ዝርዝር ሲያስቀምጥ የሽምግልና ሒደቱን ታማኝነት፣ደህንነትና ምስጢራዊነት መጠበቅ እንዲህ ባለ ጊዜ የሚያስፈልጉና በተሸምጋዮች መካከልም ቅቡል ለመሆን የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ነጥቦች መሆናቸውን ያትታል፡፡

 ገለልተኛነት ለውጤታማ ሽምግልና

ላኽዳር ብራሂሚና ሰልማን አሕመድ ሽምግልናን በተመለከተ በፃፉት መጣጥፍ የአሸማጋይ ሰባት ሐጢአቶች በሚል ያሰፈሯቸው ዝርዝሮች አሉ፡፡እነዚህም አላዋቂነት፣እብሪተኝነት፣ወገንተኛነት፣ችሎታቢስነት፣ችኩልነት፣ወላዋይነትና ሀሰተኛ ተስፋ መስጠት ናቸው፡፡

አድሏዊነት ከሁለት ወገኖች አንዱን መምረጥ ብቻ አይደለም፡፡ይህ በቀዳሚነት የተቀመጠ የሸምጋይ ሐጢአት ለሌሎቹም ሀጢአቶቾ መሰረት ነው፡፡አድሏዊ  የሆነ አሸማጋይ የሐገሪቱን ችግሮች በተመለከተ መሠረታዊ መረዳት እንዲኖረው እንኳን ፍላጎት አይኖረውም፡፡ ሸምጋዩ ወይም ሸምጋይዋ በአድሏዊ አተያይ የመረጡትን ወገን ትርክት የሚያቀነቅኑ ብቻ ሳይሆኑ የሌሎቹን ሀሳብ ለማወቅ ፍላጎት የሌላቸውና ቸልተኞች የሆኑ ናቸው፡፡  ውግንና ያለው  አሸማጋይ  ውግንና ከቆመለት  ወገን ውጭ ያሉ ሃይሎች የሚያነሱትን ምልከታ ከቁብ የሚቆጥር አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ‹‹በመጀመሪያ ችግሩን የፈጠረው እንትና ነው›› በማለት በውንጀላ የመጀመር ዝንባሌም ሊያሳይ  ይችላል፡፡ የግጭቱ ዝርዝሮች በማያስፈልጉበትና በማይጠቅሙበት ወቅት ‹‹የሚሠራውንና የማይሠራውን እናውቃለን›› በሚል ወደ ሌላኛው የሸምጋይ ሐጢአት ወደሆነው እብሪተኝነት የሚወስዱ ድርጊቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ፡፡

ቀድሞ ነገር አድሏዊ የሆነ አሸማጋይ፣ችሎታ የሌለው፣ችኩል፣ወላዋይና ሀሰተኛ ተስፋ የሚሰጥ በመሆን ሌሎቹንም የሸምጋይ ሐጢአቶች ሊቀላቀላቸው ይችላል፡፡ 
ስለዚህ አንድ ሽምግልና ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በግጭት ውስጥ ያሉ ሃይሎች ለድርድር ዝግጁ እንዲሆኑ ከመወትወት በተጨማሪ ተፋላሚዎቹ ገለልተኛ ነው ከሚሉት ድርጅት ትክክለኛና ተገቢ አሸማጋይ መመደብንም ይጠይቃል፡፡ 

ትክክለኛ አሸማጋይ ማለት በግጭት ውስጥ ባሉት ሃይሎች ዓይን የሚታመንና ገለልተኛ የሆነ ማለት ነው፡፡ ገለልተኛነት የሽምግልና ማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡የወገንተኝነት ችግር ኣድሏዊነቱ ብቻ ኣይደለም። ከኣድላዊነት ኣልፎ ወገንተኝነት ለተፈጠረው ችግር አድሏዊ ብየና በመስጠት ሽምግልናውን የሚያስተጓጉል ተገቢ ያልሆነ አጀንዳና መዋቅር ሊያዋልድ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ ለውድቀቱ መሠረት ነው፡፡

በግጭት ውስጥ ካሉት ወገኖች (ማለትም ከተሸምጋዮቹ አንዱ) መካከል አንደኛው አሸማጋዩን ውግንና አለው ብሎ ከፈረጀው የሽምግልና ሒደቱን ውጤታማ ለመሆን ይቸገራል፡፡እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥም ሊወሰድ የሚችለው መፍትሔ አዲስና ገለልተኛ አደራዳሪ መሰየም፣ አለያም ቀድሞ የተሰየመው አሸማጋይ አድሏዊ ነው ብሎ ላሰበው ተሸምጋይ ልቡ የሚራራ ሌላ ምክትል አደራዳሪ መመደብ ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ አስቀድሞ በተሰየመው አሸማጋይ የውይይቱን መዋቅር፣አካሄድና መርህ ተቀርጾ ከሆነ ግለሰቦችን መቀያየሩ በቂ አይደለም፡፡እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ከአሁን በፊት የነበረውን ጅምር ሙሉበሙሉ አስወግዶ በአዲስ መልክ እንደገና መጀመርንም ይጠይቃል፡፡ 

በኢትዮጵያ የአፍሪቃ ሕብረት ሚና እና የምርጫው ውዝግብ

 አፍሪቃ ሕብረት እና ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ የትግራዩን ግጭት እንዲሸመግሉ የሰየማቸው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የኢትዮጵያን ግጭት ለመሸምገል ያላቸው ታማኝነትና ቅቡልነታቸው መገምገም ያለባት ከላይ በተቀመጡትና በሽምግልና ወቅት በሚጠበቁት መሠረታዊ  መመዘኛዎች ነው፡፡

የአፍሪቃ ሕብረት በትግራይ ክልል ጉዳይ ውጤታማ ተሳትፎ አለማድረጉ የትኛውንም አመዛዛኝ አፍሪቃዊ ያሳዘነ ጉዳይ ነው፡፡ይህንን አሳፋሪ ዝምታ 58 ታዋቂ ኣፍሪካዊ ምሁራን እ.ኤ.አ ኦገስት 24፣ 2021 ፈርመው African Arguments  በሚባለው ድረ- ገጽ በግልጽ ያወጡትን ደብዳቤ ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ በትግራይ ስላለቁ ንፁሃን ሕብረቱ እስከ አሁን ቃል አልተነፈሰም፡፡ ከዚህም አልፎ ተጋሩ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሠራዊት፣በፖሊስ ልዩሃይሎችና ሚሊሻዎች በአስከፊ ሁኔታ ሲጨፈጨፉ፣ሴቶቹ ሲደፈሩ፣የዘር ማጽዳት ሲፈጸምባቸው፣ የአፍረቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ግን ይህንን የፈፀመውን የኢትዮጵያን መንግሥት ‹‹የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ፣ሠላምና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ስላስከበርክ እንኳን ደስ አለህ›› በማለት ሲያሞካሹት ነበር፡፡  ከዚህ አንፃር ሕብረቱ አሁን በሸምጋይነት ብቅ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በሠራው ወንጀል ምክንያት ከደረሰበት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ በዲፕሎማሲ መድረክ ለማገገም ስለፈለገ ሕብረቱን አድነኝ  ብሎ ምልጃ ልኮት ይመስላል፡፡

ባሳለፍነው ሰኔ 2013 የተካሄደውን የኢትዮጵያ ምርጫ ለመታዘብ ከመጡና አገር በቀል ካልሆኑ አካላት መካከል የአፍሪቃ ሕብረት አንዱ ነው፡፡ ምርጫው የተካሄደው ዋነኛዎቹ ተቃዋሚዎች በታሰሩበትና አገሪቱም እልም ባለ የእርስበርስ ጦርነት (በበርካታ አቅጣጫዎች) ውስጥ በወደቀችበት ወቅት ነው፡፡ በርካታ ዓለማቀፍ ተዋንያን ይህንን ምርጫ ላለመታዘብ ወስነው ቀርተዋል፡፡ለምሳሌ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ይህ ምርጫ እንዲራዘምና የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ሠላምን ማስፈን ላይ እንዲሆን ምክረሐሣብ አቅርበው ነበር፡፡ብዙ የአሜሪካ ሴኔትና ኮንግረስ አባላትም በተመሳሳይ ምርጫውን በተመለከተ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡የአውሮጳ ሕብረትም ምርጫውን ለመታዘብ ሲመጣ ሊጠቀምባቸው ስለሚገቡት የግንኙነት መሣሪያዎችና ስለ ተልዕኮው ገለልተኛነት ያስቀመጣቸው ቅድመሁኔታዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ስላልተተገበሩለት ታዛቢዎችን ለመላክ የነበረውን ዕቅድ ሰርዟል፡፡

 ምርጫው ሲካሄድ ገዥው ፓርቲ ያለምንም ተፎካካሪ በብዙ ቦታዎች በብቸኝነት ቀርቧል፡፡
ለምሳሌ በመላ ኦሮሚያ ገዥው ፓርቲ ብቻ ነው የተወዳደረው፡፡ በፌደራሉ ፓርላማ ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ ክልሉ 178 ወንበሮች አሉት፡፡በኦሮሚያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የተመዘገቡ ሁሉም ኦሮምኛ ተናጋሪ ፓርቲዎች ምርጫው ላይ ላለመሳተፍ ወስነዋል፡፡ምክንያቱም አብዛኞቹ ፓርቲዎች ወይ መሪዎቻቸው ታስረዋል፤ወይ አባሎቻቸው እየተንገላቱ ነው አለያም ቢሮዎቻቸው ተዘግተዋል፤ወይም ሁሉም ነገር ደርሶባቸዋል፡፡

 ከምርጫው መካሄድ በኋላ ለገዥው ፓርቲ ባላቸው ታማኝነት የሚታወቁት  ፓርቲዎች ሳይቀር በሂደቱም ሆነ በውጤቱ  አለመደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡እነዚህ ታማኝ ተቃዋሚዎች አምስት ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የሶሻሊስት ዴሞክራቲክ ፓርቲ በደቡብ ክልል ምርጫው እንዲደገም ጠይቋል፡፡ለዚህም ምርጫ ቦርድና የፀጥታ ሀይሎች ለገዥው ፓርቲ የሚያዳላ ተግባር ፈጽመዋል የሚልን ምክንያት አቅርቧል፡፡

ሌላኛው ለገዥው ፓርቲ ባለው ታማኝነት የሚታወቀውና የምርጫውን ሒደት የተቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው ፖለቲካዊ ድርጅት ሲሆን እርሱም ገዥው ፓርቲ በምርጫው ሰሞን በርካታ የሠራዊት መንጋ በማዘዋወር  የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በመረበሽ ምርጫው ላይ ጫና አሳድሯል ብሏል፡የምርጫ ውጤቶች ይፋ ከሆኑ በኋላም ባልደራስ ‹‹ምርጫው ነፃ፣ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም›› በማለት ደምድሟል፡፡

በምርጫው ሒደት ላይ በተለይ በአማራ፣በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች  ገዥው ፓርቲ ጣልቃ በመግባት ዜጎች ለዴሞክራሲ የነበራቸውን ተስፋ አክሽፎታል ሲል መግለጫ ያወጣው ሌላኛው የገዥው ፓርቲ ወዳጅ ተቃዋሚ ደግሞ የዐማራ  ብሐሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ- ኢዜማም ልክ እንደሌሎቹ ለገዥው ፓርቲ ባለው አጋርነት የሚታወቅ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡እርሱም በምርጫው ሒደትና ውጤት ላይ ቅሬታዎች እንዳሉት ገልፆ፣ቅሬታዎቹን ምርጫ ቦርድ ካልፈታቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ገልፁዋል፡፡የአፋር ሕዝብ ፓርቲም የምርጫውን ጠቅላላ ሒደት በመቃወም መግለጫ አውጥቷል፡፡

 የአፍሪቃ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መግለጫ የወጣው ከዚህ ሁሉ ዳራዊ ሁነት በተቃረነ መንገድ ነበር፡፡ከምርጫው ማብቃት በኋላ የሕብረቱን የታዛቢዎች ቡድን የመሩት ኦሊሰገን ኦባሳንጆ ምርጫው ተአማኒነት ባለው መልኩ መካሄዱን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ተደመጡ፡፡ኦባሳንጆ አክለውም ምርጫው እስከዛሬ ከነበሩት አንፃር ሲታይም እጅግ አሳታፊ ነበር አሉ፡፡

ይሁን እንጂ በምርጫው ዋዜማ እለትና ማግስት የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት የአማራ ሚሊሺያና ከተለያዩ ክልሎች የዘመቱ  ልዩ ሃይሎች በትግራይ ክልል ጭፍጨፋ፣ዝርፊያ፣ውድመትና አስገድዶ መድፈር እየፈፀሙ ነበር፡፡በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለ አገር የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበርም ሆኑ የታዛቢ ቡድኑ መሪ ይህንን መናገራቸው አስደንጋጭ ነበር፡፡

 ሳይጀመር የከሸፈው የሽምግልና ዕቅድ

ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕብረቱ ኦባሳንጆን የአፍሪቃ ቀንድ መልዕክተኛና የኢትዮጵያን ግጭት አደራዳሪ አድርጎ ሰየማቸው፡፡የትግራይ መንግሥት በቃል አቀባዩ በኩል እንደተናገረውና  በኋላም በትግራይ መንግስት ፕሬዚደንት በተፈረመ ይፋዊ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በላከው መግለጫ  በአፍሪቃ ሕብረት ላይም ሆነ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በተሰየሙት ኦባሳንጆ  ላይ ብቁ አሸማጋዮች ናቸው ብሎ እንደማያምን ያለውን ቅሬታ ገልፁዋል፡፡

በርግጥም የትግራይ መንግሥት ክልል ይህንን ለማለት ምክንያቶች አሉት፡፡የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የኢትዮጵያው ጠቅላይሚኒስትር በትግራይ ወሰዱት ላሉት መሠረታዊ እርምጃ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ማስተላለፋቸውና የሕብረቱ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ያወጣው መግለጫ በግልጽ የሚያሳየው ሕብረቱም ሆነ ልዩ መልዕከተኛው ውግንናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን ነው፡፡

 እስካሁን የሽምግልና ሂደቱም ሆነ ሸምጋዩ የትግራይ አመራርን አላገኘም፡፡የሕብረቱ የሽምግልና ዕቅድ ገና ከወዲሁ የከሸፈ ይመስላል፡፡የሕብረቱ ሊቀመንበርም ሆነ ልዩ መልዕከተኛው ለትግራይ ሕዝብ ሕልውና  በሚታገሉት የትግራይ ሃይሎች ዘንድ በአድሏዊነት የሚታዩ ናቸው፡፡ይህ ውግንና ደግሞ ከአድሏዊነት በላይ ሄዶ ሙከራው ሳይጀመር እንዲከሽፍ የማድረግ መዘዝ ያመጣል፡፡

ችግሩ የሚጀምረው የአፍሪቃ ሕብረት የሰኔውን ምርጫ እውቅና ሲሰጥና ያንኑ እውቅና የሠጠ ግልሰብ ደግሞ በምርጫ ምክንያት ግጭት ውስጥ የገቡትን ሃይሎች እንዲያደራድር ሲሰይም ነው፡፡ይህ የአድሏዊነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በማጭበርበር፣በማፈን፣በማስገደድና በጉቦ ውስጥ ያለፈውን “ምርጫ” ፖለቲካ እውቅና የሚሰጥም ነው፡፡ ይህንን እውቅና የሰጠ ሸምጋይ  ወደፊት ተመሳሳይ ሁኔታ ቢገጥማቸው ከዚህ በፊት እንዳደረጉት እንደማያደርጉ  ምንም መተማመኛ የለም፡፡ ሕብረቱና ዋና አሸማጋዩ የሚከተሉት  ስትራቴጂ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚከተለው አካሄድ ጋር ተመሳስሎ ያለው ይመስላል፡፡ከጠቅላይሚኒስትር አቢይ ቢሮ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እርሳቸው “ህጋዊ” የሚሉትን መንግስታቸው ከመሰረቱ በኋላ ከተወሰኑ የትግራይ ሰዎች ጋር ለመነጋገርና በሚመሰርቱት መንግሥት ውስጥ የተወሰኑ ሹመቶችንም እሰጣለሁ ብለው ለመደራደር እንደተዘጋጁ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሉአላዊነትን የህዝብንና የአገርን ድህንነት ከመጠበቅ ሃላፊነት ጋር አስተሳስረው አይመለከቱትም፡፡ ለአቢይ ሉአላዊነት ገዥዎች የፈለጉትን ከሚያደርጉበት የነጠላ ሃላፊነት የተለየ ይዘት የለውም፡፡ ይህ አመለካከት በ1970ዎቹ  የቀረው ሉአላዊነትን የገዥዎች መቅጫ ብትር አድርጎ የሚመለከተውን አስተሳሰብ ያስታውሰናል፡፡ ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያ ገዥዎች “ስዩመ እግዚ አብሄር ነን፣ ሉ አላዊነት ማለት እኛ ነን›› ይሉ የነበሩበት ጊዜንም ያስታውሰናል፡፡ አደጋውን ከፍተኛ የሚያደርገው ይህ የተዛባ የአብይ የሉአላዊነት አመለካከት የፖለቲካ ድርድርን እንደ የገበያ የዋጋ ድርድር  አድርጎ የሚመለከትና ሁሉንም ነገር በጥቅምና በገንዘብ መግዛት የሚቻል አድርጎ ከሚመለከት አተያያቸው ተጣምሮ መገኘቱ ነው፡፡

በዚህ አመለካከት መሰረት የትግራይ ችግር የትግራይ ልሂቃን በስልጣን ክፍፍል ከሚያነሱት  የይገባኛል ጥያቄ የዘለለ አይደለም፡፡ ይህ የችግር አረዳድ ቅጥረኞችን የማስተዳደር ዘይቤን ይጎትትና ጥረቱ ከመንግስት ጋር ተዋህዶ ግጭቱን ለማቆም እያንዳንዱ ልሂቅ የሚጠይቀውን ዋጋ ለማወቅ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ፍለጋ ወደ 1945 እንመለስ፡፡በወቅቱ በፌደሬሽን ትተዳደር የነበረችውን ኤርትራን አፍርሰው በንጉሳዊው አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ የተደረገችበት አካሄድ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

አንድ ሸምጋይ  የግጭቱን ወገኖች መምረጥ አይችልም፡፡ ሁሉንም እውቅና መስጠት እና ሁሉንም ከመጀመሪያው ጀምሮ ማሳተፍ አለበት። ማንኛውም ለሽምግልና የሚቀመጥ አካል ተደራዳሪዎቹን እንዳሉበት የመቀበልና የድርድሩን አጀንዳዎች ለማንጠርና አካሄዱን ለመወሰን በሚያደርገው ጥረት ሁሉንም በእኩልነት ተመልክቶ የማነጋገር ሃላፊነት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “አዲሱ መንግሥታቸውን” ከመሰረቱ በኋላ እራሳቸውን ‹አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት› ብለው መጥራት ይፈልጋሉ፡፡ አደራዳሪው ይህንን ከተቀበለ የትግራይ ክልላዊ መንግስት እራሱን የትግራይ መንግሥት ብሉ ሲጠራ እሱንም የመቀበልና በስሙ የመጥራትም ግዴታ አለበት፡፡

 ይሁን እንጂ ሕብረቱ እየተከተለ ያለው የጠቅላሚኒስትር ዐቢይን እቅድ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ሕገመንግሥታዊና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ስለሆነ ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ አይቀየርም የሚል ሥሌት ይዞ ለመቅረብ ከሕብረቱ ደንቦች አንዱን ሊመዝ ያሰበ ይመስላል፡፡ስለዚህ መንግሥትን ከአማጽያን ጋር ለማደራደር የሚሠራ  አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል፡፡እንዲህ ያለው አላዋቂነት የሕብረቱን መሠረታዊ መርህ ማለትም የጦር ወንጀል መፈጸምን፣በሰብአዊነት ላይ ወንጀል መፈጸምንና ዘር ማጥፋትን የሚያወግዘውን ደንብ የሚዘነጋ ነው፡፡

 በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት ግለሰቦችን ከማባባል በላይ ነው፡፡ሕብረቱ በሽምግልና መርሆች ላይ ተመስርቶ ሽምግልናውን ያካሂድ ይሆን የሚለው እስካሁን አልታወቀም፡፡

 የጦርነቱ ሥረ መሠረት የፌደራሉ መንግሥት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ንዶ፣ንጉስ መሣይ አሐዳዊ አገዛዙን ዘርግቶ ለመኖር ከማለም የሚነሳ ነው፡፡ይህንን ግን ትግራይ እምቢ አለች፡፡ሕገመንግሥቱ ይከበር ብላ ወሰነች፡፡ይህ የጦርነቱ መጀመር ዋና ምክንያት ነው፡፡  አሁን ሁለቱም መንግሥታት አንዱ ሌላኛውን እውቅና አይሰጠውም፡፡የድርድር ሂደት የሚጀመረው ደግሞ ቢያንስ እርስበርስ ለመነጋገር ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ይህ ደግሞ የድርድር መርሆችን ማስቀመጥን ይጠይቃል፡፡

የትግራይ ክልል መንግሥት የፌደራሉ ሕገመንግሥት የድርድሩ መነሻ እንዲሆን ፍላጎት አለው፡፡በአንፃሩ ሕገመንግሥታዊነት የማዕከላዊ መንግሥቱ ዋና ጉዳይ አይደለም፡፡  ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የትግራይ ሕዝብ ሕልውና ነው፡፡የአዲስ አበባው መንግሥትና አጋሮቹ መሰረታዊ የጦርነት ሕጎችን ጥሰው በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት አውጀው ተግብረዋል፡፡ይህ ጉዳይ በቅጡ ካልተነገረና እንደ ጉዳይ ካልተያዘ ጦርነቱ ሊቆም አይችልም፡፡ይህንን ዘር ማጥፋት የፈፀሙ ሃይሎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፤ጉዳዩም እንደ ዋና አጀንዳ መታየት አለበት የሚለው ለትግራይ መንግሥት መሠረታዊ ነው፡፡

 የግጭቱን ምንነት በመለየት እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች ግምት ውስጥ የማያስገባ ሽምግልና ገና ያልተጀመረ ይሆናል።ዐቢይ የአገርን ሉዓላዊነት እንደ ግዴታው አያየውም፡፡በተደጋጋሚ የዓለማቀፉን ማሕበረሰብ የሚከሰው የአገሬን ሉዓላዊነት ደፈራችሁ እያለ ነው፡፡በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አገልግሎት ሃላፊዊችን እስከማባረር ደርሷል፡፡ የሆነው ሆኖ ዘላቂ መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ የሽግግር አስተዳደርን ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

 ለማጠቃለል ተጋሩ በአፍሪቃ ሕብረት የሽምግልና እቅድ ላይ ያላቸው ቅሬታ ሃላፊነት የሚሰማቸው ዐለማቀፍ አካላት ትኩረት እንዲያደርጉበትና መፍትሄ እንዲፈልጉለት የሚያደርግ ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ፣የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂም ሆኑ የሕብረቱ ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት የሚታመኑ አይደሉም፡፡  እናም ጉዳዩ ያሳሰባቸው አገራትና ዓለማቀፍ ተቋማት መርህ ተከል የሆነ፣መዋቅራዊነቱን በጠበቀና የአደራዳሪነት አቀራረብን ባማከለ ሁኔታ ቢገቡበት መልካም ይሆናል፡፡

ይህ ጽሁፍ በ World peace foundation ድረገጽ ላይ የቱፍትስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ሙሉጌታ ገብረሕይወት Not Impartial, Not Principled, Non-Starter: African Union Mediation in Ethiopia በሚል ርዕስ ያስነበቡት ጽሁፍ ሲሆን ወደ አማርኛ እንዲመለስ ያደረጉት ደግሞ አገኘሁና ንጉሱ ናቸው፡ዋናውንና የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ በሚከተለው ሊንክ ያገኙታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: